ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ

በ1908 ዓ.ም. በሮም ባሳተሟት ልቦለድ ታሪክ የፈጠራ ሥራቸው-በኢትዮዽያ የአማርኛ ዘመናዊ ሥነጽሑፍ መሥራች ካሰኛቸው ማእረግ ባሻገር በአፍሪካ ቋንቋዎችም ታሪክ- በሀገርኛ ቋንቋ በመጻፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የሚል ምስክርነት አግኝተዋል። ደራሲው ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ሲሆኑ የልብወለድ ድረሰታቸው ‘ጦቢያ’ ትባላለች። ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ በደቡባዊ የጣና ሐይቅ ደሴት ክፍል በምትገኘው ዘጌ በሐምሌ ወር 1860 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በታዋቂው አያታቸው በመምህር ድንቄ ጠባቂነት በአካባቢው በምትገኘው ኡራ ኪዳነምህረት ቤተ ክርስትያን የተለያዩ ሀይማኖታዊ ትምህርቶችን እየተከታተሉና ጎን ለጎንም በአካባቢው በስፋት በሚዘወተረው የባህላዊ ስእል ስራ ላይ እየተሳተፉ አደጉ፡፡ ከ1872 ዓ.ም በኋላ በእቴጌ ጣይቱ አማካኝነት አፈወርቅ ገብረ-ኢየሱስ ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር እንዲተዋወቁ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜም አፈወርቅ የኢጣሊያ መልእክተኛ ከሆኑት ከካውንት ፔትሮ አንቶሎኒ ጋር የመተዋወቅ እድል አገኙ፡፡ መልእክተኛው አንቶኖሊም በአፈወርቅ የስነ ጥበብ ዝንባሌ በመደነቅ አፈወርቅን ወደ ኢጣሊያ ወስደው ለማስተማር ለዳግማዊ ምኒልክ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ይኸው ተፈቀደላቸው፡፡

በመስከረም ወር 1880 ዓ.ም አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ የመጀመሪያቸው የሆነውን ጉዞ ወደ ኢጣሊያ አደረጉ፡፡ በኢጣሊያ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበልም ለዲፕሎማቲክ መልእክተኛ የሚደረገውን አቀባበል ይመስል ነበር፡፡ አፈወርቅ ከኢጣሊያው ንጉሥ ኡምቤርቶ ቀዳማዊ ጋር በመገናኘት ከዳግማዊ ምኒልክ የተላከውን ስጦታ ለኢጣሊያው ንጉሥ አስረክበዋል፡፡ አፈርቅ በኢጣሊያ ከደረሱ በኋላ በቱሪን በሚገኘው አለምአቀፍ ኢንስቲትዩት የአልበርቲና የስነ-ጥበብ አካዳሚ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ተደረገ፡፡ በ1896 ዓ.ም አፈወርቅ በቱሪን የተዋወቋትን ኡጌኒያ ሮዚን አገቡ፡፡ በኔፕልስ በቆዩባቸው ከ1896 ዓ.ም እስከ 1904 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ጦቢያ የተሰኘውን የልቦለድና ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተሰኘውን የታሪክ መጽሀፍት አዘጋጁ፡፡ የኢጣሊያ-አማርኛ የንግግር ዘይቤና የተጓዦች መመሪያ የተሰኙት ጽሁፎችን አፈወርቅ ያዘጋጁትም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡

በ1904 ዓ.ም አፈወርቅ በኤርትራ የኢምፖርት-ኤክስፖርት ድርጅት በማቋቋም ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ ተጠጉ፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ሞትና የወጣቱ የልጅ ኢያሱ የምኒልክ አልጋ ወራሽ መሆን አፈወርቅ ኑሮን በአዲስ መልክ በኢትዮጵያ እንዲጀምሩ ተስፋ ስለሰጣቸው ልጅ ኢያሱን የሚያሞግሱ ግጥሞችንም መጻፍ ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ልጅ ኢያሱ አለመታደል ሆኖ በአገር ውስጥና በውጭ ጠላቶቻቸው ትብብር በ1908 ዓ.ም ከስልጣን በመወገዳቸው የስልጣን ጊዜያቸው አጭር ሆነ፡፡ በ1910 ዓ.ም በራስ ተፈሪ መኮንን ግብዣ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ገቡ፡፡ በመጀመሪያ ሹመታቸውም በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ የንግድ ልዑክ ሆነው እንዲያገለግሉ ተደረገ፡፡ ከዚህ በመቀጠልም የምስራቅ ኢትዮጵያዋ ጠቃሚ የንግድ ከተማ የሆነችው የድሬደዋ ነጋድራስ ሆነው የተሾሙ ሲሆን ከ1917 ዓ.ም እስከ 1922 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በውጭ አገር ሰዎችና በኢትዮጵያውያን መካከል ያሉ ክርክሮችን እንዲዳኝ የተቋቋመው ልዩ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው በመሾም በከፍተኛ ታታሪነት አገልግለዋል፡፡

በ1928 ዓ.ም የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት ሲጀመር አፈወርቅ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ ይህንንም አንዳንድ የነጋድራስ አፈወርቅ ደጋፊዎች የአርበኝነታቸው ማረጋገጫ እንደሆነ አድርገው አቅርበውታል፡፡ ጣሊያኖች አዲስ አበባን እንደተቆጣጠሩ ግን ነጋድራስ አፈወርቅ ያለምንም መሸፋፈን የኢትዮጵያን በኢጣሊያ ቅኝ መገዛት በአደባባይ መደገፍ ጀመሩ፡፡ በስደት ወደ ውጭ የሄዱትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴንና በዱር በገደሉ ፋሽስት ኢጣሊያን ሲዋጉ የነበሩትን የኢትዮጵያ አርበኞችንም መርዘኛ በሆኑ ቃላት ማንኳሰስ ጀመሩ፡፡ በ1933 ዓ.ም የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ተሸንፎ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ አገር እንደተመለሱ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ-ኢየሱስ በአገር ክህደት ተከሰው የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሞት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀልላቸው ተደርጎ ነጋድረስ አፈወርቅ በጅማ የእስራት ጊዜያቸውን በመፈጸም ላይ ሳሉ አይናቸው ታውሮ በመስከረም ወር 1940 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ

ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ ሲታወሱ፤ ከነሙሉ ግርማ ሞገሱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ በመጣው ዘመን አይሽሬ ፍቅር እስከ መቃብር መፅሀፋቸው ይሞገሳሉ።

ደራሲ ሀዲስ አለማየው በማይነጥፈው ብዕራቸው የአንባቢያን ልብ ውስጥ የቀሩ ትዝታ፣ የልምዣት፣ ወንጀለኛው ዳኛ እና ሌሎች ተወዳጅ መፅሀፎችንም ፅፈዋል።

የክብር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ዕድገት ታሪክ ላይ ልዩ ስፍራ አላቸው።

ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ ከዘመናት በፊት ከኢቢሲ ፊለፊት ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ "ፍቅር እስከ መቃብርን የፃፍኩት ሰዎች ፍቅር ሲሰማቸው የሚናገሩትን የሚያደርጉትን እኔ ከማደርገው እና ከምናገረው ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ስላገኘውት በሚዋደዱ መሀል የሚፈጠር መሆኑን ስለተረዳው በዚሁ መንፈስ የፃፍኩት ነው" ብለዋል። በፅሁፋቸው የአንባቢያንን ልብ የገዙት ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ፤ አንድ ደራሲ የሰማውን ብቻ ከሚፅፍ የደረሰበት እና ያለፈበትን የህይወት ተሞክሮ መፃፉ የበለጠ ተሰሚነት እና ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳዋል ሲሉ መክረዋል።

ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ ከአባታቸው የኔታ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ከእናታቸው ደስታ አለሙ በደብረ ማርቆስ አውራጃ በእንዶዳም ኪዳነምህረት ነው የተወለዱት። የልጅነት ህይወታቸውን በትምህርት ያሳለፉት ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ፤ ከዘመናዊው ትምህርት በተጨማሪ ጎጃም ውስጥ በሚገኙ ገዳማት እና አድባራት መንፈሳዊ ትምህርት ተምረዋል።

የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ከደራሲነታቸው ባሻገር ለሀገራቸው በመምህርነት፣ በዲፕሎማትነት እንዲሁም በአርበኝነት በመስራት የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በትምህርት ሚኒስተር፣ በአምባሳደርነት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር፣ በልማት ሚኒስትር፣ በሌሎችም ተቋማት ያገለገሉ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሥነ-ፅሁፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጋቸው የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንቱታን ያተረፉ በተለይ በፍቅር እስከ መቃብር መፅሀፋቸው ዝነኛ የሆኑ ታላቅ የሥነ-ፅሁፍ ሊቅ የክብር ዶ/ር ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ የተወለዱት በ1902 ዓ.ም ነበር።

ትላንትን የጻፉ፣ ዛሬን ያሳዩ"

"Who wrote yesterday, to show us today."