ደራሲ ዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ

ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍና የፎክሎር ተመራማሪ ዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ፣ ውልደቱም እድገቱም ወልቂጤ ነው፡፡ በወልቂጤ ከተማ ውስጥ፣ የመጀመርያና የመለስተኛ ደረጃ ትምሕርቱን በራስ ዘሥላሴ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ደግሞ በጎሮ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ያገባደደ ሲሆን፣ በ1990ዎቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ዲፕሎማ ከዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፣ በቴአትር ጥበባት ትምሕርት ባችለር ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በዚሁ ዩኒቨርስቲ በሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምሕርት ዘርፍ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪውን (Phd.) ይዟል፡፡

እስካሁን ድረስ፣ ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን ከሠራቸው፣ በአርታኢነት ከተሳተፈባቸው መጻሕፍት ሌላ (‹‹ደቦ - ቅጽ 1›› እና ‹‹ደቦ - ቅጽ 2››ን ልብ ይሏል) በግሉ፣ ከ1996 – 2013 ባሉት ዓመታት፣ አስራ ሦስት መጻሕፍትን ያስነበበ ትጉ ደራሲ ሲሆን፣ ሥራዎቹም በአራት ይመደባሉ፡፡ እነዚህም (1) አጫጭር ትረካዎች (‹‹ከጥቁር ሰማይ ስር›› - 1996፣ ‹‹የመኝታ ቤት ምስጢሮች›› - 2000፣ ‹‹ጽላሎት›› - 2004፣ ‹‹መክሊት›› - 2012) (2) ረጃጅም ልቦለዶች (‹‹ዛጎል›› - 1998፣ ‹‹ደርሶ መልስ›› - 2001፣ ‹‹እምቢታ›› - 2006፣ ‹‹ምሳሌ›› - 2010) (3) ኢ - ልቦለድ ሥራዎች (‹‹ኬር ሻዶ›› - 2001፣ ‹‹ማዕቀብ›› - 2006፣ ‹‹በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ› ›- 2006 እና ‹‹ያልተቀበልናቸው›› - 2009) (4) የግጥም ስብስቦች (‹‹ልብ ሲበርደው›› - 2001) ናቸው፡፡ እንዳለጌታ፣ በወልቂጤ ከተማ፣ በ1989 ዓ.ም፣ ‹‹ተስፋ መጻሕፍት ቤት›› የተሰኘ ማዕከል ከፍቶ፣ ለሃያ አራት ሰዓት ሃያ አምስት ሳንቲም እያስከፈለ፣ የማንበቢያ ቦታ እያመቻቸ፣ አንጋፋ ደራስያን ከከተማው ነዋሪዎችና አድናቂዎቻቸው ጋር እንዲገናኝ እያደረገ፣ የሥነ ጽሑፍ ውድድር እያዘጋጀ፣ በርካቶችን በንባብ አንጾና በሚከተለው የጥበብ ,ፈለግ ተከታይ ማፍራት የቻለ ደራሲ ነው፡፡

እንዳለጌታ ለሥነ ጽሑፍና ለንብብ መዳበር ባበረከተው፣ በወጣቶችና በልጆች ሥነ-ምግባራዊ ዕድገት ላይ ባበረከተው አስተዋጽዖ ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና የምስክር ወረቆቶችን ከተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት የተቀበለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል፣ በ2005 ዓ.ም ያገኘው ‹‹ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት›› እጅጉን ይታወቃል፡፡ እንዳለጌታ፣ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባነት፣ በዚሁ ዩኒቨርስቲ በተቋቋመውና በክቡር ደራሲ ከበደ ሚካኤል ስም በተሰየመው የባሕል ማዕከል ውስጥ በዳይሬክተርነት፣ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በዋና ጸሐፊነት (ከ1997-2005 ድረስ፣ በነጻ) እንዲሁም፣ በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ውስጥ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ውስጥ በመስራችነትና በዳይሬክተርነት ለአራት ተከታታይ ዓመታት አገልግሏል፡፡ እንዳለጌታ በአሁኑ ወቅት፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በፈረንሳይ ለጋሲዮን ሲያደርገው ቆይቶ በሁኔታዎች አለመመቻቸት አቋርጦት የነበረውን ተግባር በማዘመን፣ የተለያዩ ጥበባት የሚከወኑበት፣ ከያንያን ራሳቸውን የሚገልጹበት ‹‹ዛጎል ቤተ ጥበባት›› የተሠኘ ድርጅት ከፍቶ፣ በሥሩም ‹‹ቡክ ባንክ›› በማቋቋም ንባብና አንባቢ በመላ ኢትዮጵያ እንዲደረጅ፣ መጻሕፍት ቤት እንዲስፋፋና መጠየቅና ማሰላሰል የሚችል ዜጋ በመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል ።

ደራሲ አዳም ረታ

አዳም ረታ በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። በትምህርት አለም - በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል። ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪውን ደግሞ በውጭ ሀገር አግኝቷል። የሚፅፈው በአብዛኛው ልቦለዶችን ቢሆንም ግጥሞችንም ይፅፋል። በተለያዩ ጊዜያት ግጥሞቹ በተለያዩ መፅሔቶች ላይ ታትመዋል።

በ1981 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ የታተመው “ማህሌት” የደራሲው የመጀመሪያ ወጥ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መፅሀፍ ነው። በሻማ ቡክስ በ1997 ዓ.ም የታተመው “ግራጫ ቃጭሎች” እንደ ብሉይ (classic) ሥራ ሊታይ የሚችልና የደራሲው ልዩ ብቃት የታየበት ወጥ ረጅም ልብወለድ ነው።
በ2001 ዓ.ም ሁለት ልዩ ስራዎች ይዞ የቀረበው አዳም፡ የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ የሆነው “አለንጋና ምስር” እና እርስ በርሳቸው በቀጭን የታሪክ ክር የሚገናኙ ልብወለዶች (ኖቬላዎች) ያካተተው “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ለአንባቢያን አበርክቷል። ይህ የአጻጻፍ ስልቱ ሕጽናዊነት ሲሆን ደራሲው በሌሎቹ መጻሕፍቱም ውስጥ በስፋት ተጠቅሞበታል፡፡

ቀጠሉት ሦስት ዓመታት በየዓመቱ አንዳንድ መፅሐፍ ለአንባቢያ ያደረሰ ሲሆን በ2002 ዓ.ም “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር”፣ በ2003 ዓ.ም “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” እና በ2004 ዓ.ም “ሕማማት እና በገና” ታትመው ለንባብ በቅተዋል። “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” በተሰኘው መፅሀፉ ድንቅ የፋንታሲ (“ፈንጠዚያ”) ሥራዎች የተካተቱ ሲሆን በ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ለመጀመሪያ ጊዜ መቼቱን ከሀገር ውጭ በማድረግ የውጭውን ሕይወት በስሱ የዳሰሰ ሲሆን ከሌሎቹ ስራዎቹ በተለየ መልኩ ስለሀገራችን ፖለቲካ ወጣ-ገባ መንገድ በታዛቢ አይን ምልከታው፣ ትውስታውን … አስፍሯል፡፡ ሕማማትና በገና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆን ለየት ያለ ቅርፅ ያላቸው አንዳንድ ልቦለዶች ተካተውበታል።

አዳም ረታ በተለየ የአፃፃፍ ስልቱ እና በስራዎቹ ጥልቀት በሃያስያን ዘንድ አዎንታዊ ሂስ እና ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።

…ዳኛቸው ወርቁ በ“አደፍርስ” የኢፒሶዲክ ሕግጋትን አጋምሶ ለማስተዋወቅ ከሞከረ ወዲህ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በኢፒሶዲክ ተሟልቶ የተገኘ ድርሰት “ግራጫ ቃጭሎች” ነው። … “ግራጫ ቃጭሎች” ከገፀ-ባህሪው አካልና ሥነ-ልቡና አሳሳል አልፈን ድንቅ ዓላማውን፣ ቋንቋውንና የሕይወት አተረጓጎሙን ስንመለከት የአዳም ረታ እውቀትና ልምድ ጠንከር - ጠጠር ብሎ በመዝገቡ በኩል ሲያስተጋባ ነው የምንመለከተው።

"ከቃል በላይ... ትውልድ ተሻጋሪ"

"Beyond words... spanning generations."