ተማሪና ገጣሚ ረድኤት አብርሀም

ውሸት ታንቆ ይሙት

ምድር ላይ ካሉ ሰዎች እርስ በርስ ከተለያዮ፤

አድገናል የሚሉ እውነትን እያዮ፤

ውሸት አናውራም ሀሰት ቆይ ለምኔ

እያሉ እውነትን ተው ላውራት እኔ፤

እኔ ግን ወንድሜ ከእውነት እርቄያለው

መተዳደሪያዬን ሀሰት አድርጌያለው፤

አንድ ይቺ ምላሴ የአካሌ ክፍል

ሀሰትን ደብቃ እውነት እውነት ብትል

መገደሌ አይቀርም ሀሰትኮ ከሚል ፤

ስለዚህ ከሀቀኛ ነን ባዮች

ከሚሉ ለእውነት በእውነት ነን ሟቾች ፤

ውስጣቸው እንደሞላው እያወክ ሀሰት

አሜን ብለህ ትኖራለህ እንድትቆይ በህይወት፤

ሀቅን ብትል ፈራጁ ይበዛል ባዩ ይሄ ይሙት

እውነት አያዋጣም ውሸት ታንቆ ይሙት ።

ተማሪና ገጣሚ ረድኤት አብርሀም አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ኮተቤ ወረዳ ፲ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ 2000 ዓ ም ተወለደች። እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰም ሰርድ ጄኔሬሽን መዋዕለ ህፃናት ገባች። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም እዛው አጠናቀቀች ። በመቀጠልም የደረጃ ፩(1) ትምህርቷን ቅዱስ ሚካኤል የተሰኘው ትምህርት ቤት ተማረች ። በተለያዩ የሁኔታዎች አለመመቻቸት የደረጃ ፪(2) ትምህርቷን ሜንተር ከዛም ኖኤል ቀጠለች። ታድያ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ የስነ ፅሁፍ መድረክ ላይ መሳተፍ ያስደስታት ነበር ። ይህ ትንሽ ደስታ እያደገ እያደገ ትልቅ የስነ ፅሁፍ ባለሞያ የመሆን ፍላጎት እያሳደረባት መጣ ። በተለይም ለግጥም ያላት ፍቅር ከእለት እለት እየጨመረ በመምጣቱ የተለያዩ ግጥሞችን እንድትፅፍ አድርጓታል። ይህች ታዳጊ ገጣሚ የተለያዪ መድረኮች ላይ ግጥሟን ለማቅረብ እድል አግኝታለች የተወሰኑ መድረኮች ላይም ለማቅረብ ችላለች። አሁን የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በአሁኑ ት/ቤቷ ሐርመኒ ሒልስ አካዳሚም ቢሆን ባለፈው ዓመት የወላጆች በዓል ላይም በአማርኛ መምህሯ አማካኝነት ባገኘችው እድል የግጥም ስራዎቿን በመድረክ ላይ ለማቅረብ ትችላለች።

ግጥምን እንዲህ ትገልፀዋለች ግጥም ለመፃፍ የመጀመሪያው ካነሳሱኝ ነገሮች አንዱ በውስጤ ያለው ስሜት እና ፍላጎት እንዲሁም የሚሰጠኝ ሰላም ነው ። ግጥም ስሜቴን ለመግለፅ የተሰማኝን ነገር በብዕር ለወረቀት የማቀብልበት መንገድ ነው ። በቀን ውሎዬ ውስጥ የማየውን ፣ ከአለም የምታዘበውን የምገልፅበት ፣ ለሰው መግለፅ ያቃተኝን ትልቁን ስሜቴን ቃላቶች አሰባስቤ ትርጉም ወዳለው ነገር የምቀይርበት መንገድ ነው ።

የወደፊት ህልሜ፤ በግጥም ኢንዱስትሪው ውስጥ እጅግ ስኬታማ ገጣሚ በመሆን፣ ጥልቅ ስሜትንና ማህበራዊ እውነታዎችን የሚዳስሱ ጠንከር ያሉ የግጥም ስራዎችን ለሰፊው ተደራሲያን በማድረስ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ነው። በተለይም ጥንቅራቸው የታለሙና መልዕክት አዘል የሆኑ ስራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰራጨት፣ በኪነ-ጥበብ ስሜትና ጥበብን በሚያከብር ማህበረሰብ ዘንድ የማይደበዝዝ አሻራ ጥሎ ማለፍ ትልቁ ግቤ ነው "ትላለች" ።

ከንቱ

ጫጫታው ብዙ ነው በአለም ላይ ያለው

ሰው ሁሉ ያወራል ግን ቁም ነገር የለው

ወዲያ ወዲህ ይላል አንድአንዱ ይሰራል

ግማሹ አመስጋኝ ሌላው ያማርራል

አንዱ ጠግቦ ሲያድር አንዱ ደግሞ ይራባል፤

ሰው ከንቱ መሆኑን እያስመሰከረ ቁም ነገር ሳይሰራ ስንቱ ተባረረ፤

የእንቆቅልሹን መልስ ማንም ሳይረዳው ይወጣል ይወርዳል ሚስጥሩን ሳይፈታው።