ከበደ ሚካኤል


ከበደ ሚካኤል (1909-1991) በደብረ ብርሃን ከተማ፣ ገርም ገብርኤል አጥቢያ ጥቅምት 23 ቀን 1909 ዓ.ም.ተወለዱ። ወደ አዲስ አበባ እንደ መጡ መጀመሪያ በአሊአንስ ኢቲዮ-ፍራንሴዝ በኋላም በላዛሪስት ሚሲዮን ትምህርታቸውን ተከታተሉ። የሼክስፒርን ሮሜዎና ዡልየትን ማክቤዝን በመተርጎም እውቅናን ለማትረፍ ችለዋል።

ከበደ ሚካኤል 30 ገደማ መፃሕፍትን ፅፈዋል። ከበደ ሚካኤል በርካታ የስነ ጽሁፍ ስራዎች ባለቤት በመሆናቸው በተለይም ለልጆች ትምህርት አዘል ጽሁፎችን የግጥም የፈጠራ ስራዎችን ቅኔዎችን በስፋት በማበርክታቸው በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ መድረክ ገናና ከሆኑት ደራሲዎች አንዱ ናቸው።

የሰዎች ስነ ምግባር ላይ የማተኮርና ምክር አዘል መልእክቶችን የማስተላለፍ ዝንባሌአቸው በአብዛኛው ስራቸው ላይ ይንጸባረቃል። ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለማደርጀት በተደረገው ትግል በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ እኒህ ፈላስማ፥ ባለቅኔ፥ ጸሐፌ-ተውኔት፥ ደራሲና አንጋፋ ጋዜጠኛ ፥ የቀለም ሰው በሀገራችን የመጀመሪያ የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በቀዳሚነት የተቀበሉ ሲሆን፣ አዲስ ትውልድ ላፈራ ስብእናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 26 ቀን 1990 ዓ.ም. በሥነ ጽሑፍ የክብር ዶክቶሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል። በተረፈም ከፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሶቭየት ህብረትና ሜክሲኮ ሽልማትን ተቀብለዋል።

በተረፈ የትምህርት ሚኒስትር ዳይረክተር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተከታይ ዳይሬክተር (1942)፣ የብሄራዊ መጻህፍት ቤት ዳይረክተር (1944)ና የካቢኔ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል። ክቡር ዶክቶር ከበደ ሚካኤል፥ ኢትዮጵያዊ የቀለም ሰው ኅዳር 3 ቀን 1991 ዓ.ም. በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው አረፉ።

    ያበረከቱት የሥነ-ጹሑፍ ስራዎች

  • የትንቢት ቀጠሮ (ሥነ-ግጥም መማሪያ መጽሀፍ) 1938
  • ሮሚዎና ዡሊየት (ተውኔት ትርጉም) 1946
  • ታላላቅ ሰዎች (ኢ-ልብወለድ) 1943
  • የዓለም ታሪክ (ኢ-ልብወለድ) 1956
  • አኒባል (ተውኔት-በግጥም) 1956
  • የቅጣት ማዕበል (ተውኔት-በግጥም) 1951
  • ሄሮዶተስ (ኢ-ልብወለድ-ትርጉም)
  • ታሪክናምሳሌ (መማሪያ መጽሀፍ) 1934
  • ጃፓን እንዴት ሰለጠነች (ኢ-ልብወለድ) 1946
  • የዕውቀት ብልጭታ (ኢ-ልብወለድ) 1939
  • ካሌብ (ተውኔት) 1958
  • ኢትዮጵያና ምዕራባዊ ስልጣኔ (ኢ-ልብወለድ) 1941
  • የኀሊና ደወል
  • ብርሃንና ኅሊና (ሥነ-ግጥም) 1933
  • የኢትዮጵያ የጥንት ሥዕሎች 1961
  • አክአብ (ተውኔት)
  • ሥልጣኔ ምንድነች? (ኢ-ልብወለድ)
  • የቅኔ ውበት (ሥነ-ግጥም) 1957

ዓለም ና ጊዜ

አንዱ ስፍራ ሲለቅ አንዱ እየተተካ፥

ሁሉም ርስቴ ነች እያለ ሲመካ፣

ሞኝነት አድሮብን ሳናሰበው እኛ፥

ዓለም ሰፈር ሆና ሕዝብ መንገደኛ፥

ትውልድ ፈሳሽ ውሃ መሬቷም ዥረት፣

መሆኑን ዘንግቶት ይህ ሁሉ ፍጥረት፥

ስትመለከቱት በሰልፍ ተጉዞ ፣

ሁሉም በየተራው ያልፋል ተያይዞ ።