ገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ

ገብረ ክርቶስ ከአባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ እና ከእናቱ ከወ/ሮ አፀደ ማርያም ወንድማገኝ በ1924 ዓ.ም በምስራቁ የሀገራችን ክፍለ ሀረር ከተማ ተወለደ፡፡ ከዘር የሚወረስ አንዳች ነገር ካለ አባቱ አለቃ ደስታ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሀይማኖታዊ ትምህርት ሊቅና በብራና የእጅ ጽሁፎቻቸው በባህላዊው ሥዕሎቻቸው የተደነቁ ሰው እንደ ነበሩ ይነገራል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ወላጅ እናቱን (ወ/ሮ አፀደ ማርያም ወንድማገኝ) ገና በልጅነቱ በሞት ተነጠቀ፡፡ መቸም የእናት ሞት ከባድ ነው፡፡ ብቻ አምላክ ጨርሶ አልከፋም አያቱ እማሆይ ብርቅነሽ ሳሳሁ ልክ እንደ እናት ማስረሻ… ልክ እንደ እናት ሆነው አሳደጉት፡፡

ገብረ ክርስቶስ ለአባቱ የነበረው ፍቅር መቸም የተለየ ነው፡፡ ይህንንም አድናቆቱን ”እረፍት አድርግ አሁን” በሚለው ግጥሙ ገልፆታል፡፡ አንጀት የሚበላ ግጥም ነው! ገብረ ክርስቶስ 1961 ከ ሄድ ሲድኒ ጋር ባደረገው አጭር ቃለ መጠይቅ ስለ አባቱ የሚከተውን ብሎ ነበር፡- አበቴ ቅዱሳን መጻህፍትን በእጁ ይጽፍ ነበር፡፡ በዘመኑ ዘመናዊ የህትመት መሳሪያ በሀገራችን የነበረ ቢሆንም በኖረው ባህል መሠረት በእጅ የተዘጋጁ መጻህፍት ተመራጭ ነበሩ፡፡ ለመጸሀፍቱ ዝግጅት የሚያስፈልገውን መጻፊያም ሆነ ቀለሙን ያዘጋጅ የነበረውና እራሱ ሲሆን፤ በቅዱሳን መጻህፍቱ ውሥጥ የሚካተቱ ምስሎችን ይሠራ ነበር፡፡ በልጅነት ጊዜዬ የአባቴን ሥራዎች እያየሁ እደነቅ ነበር፡፡ በየቀኑ ሥዕል እንድሠራም ያበረታታኝ ነበር፡፡

ገብረ ክርስቶስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማው ሐረር ራስ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ ሲያጠናቅቅ ለሁለተኛና ለከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱ አዲስ አበባ ተቀበለችው፡፡ ሸገር የሁሉም አድባር! እንደመጣ በቅድሚያ የተመደበው በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ (በዛ ዘመን በንጉስ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ ለባለ ብሩሕ አእምሮ ተማሪዎች ከተዘጋጁት የትምህር ተቋማት መካከል ኮተቤና ጄኔራል ውንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ልብ ይሏዋል) በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ አጭር ቆይታው በኢትዮጵያ የጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ዝና ያላቸውን ስመጥሮቹን በተለይ መንግስቱ ለማንና አፈወርቅ ተክሌን የመተዋወቅ ዕድል አግኝቷል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ሳይንስ ፋካልቲ የተመደበው ገብረ ክርስቶስ ትምህርቱን የተከታተለው ለአጭር ጊዜ ነበር፡፡

ገብረ ክርስቶስ በግጥሙ በይበልጥ የታወቀው ከ1959 ዓ.ም ጀመሮ ሲሆን በተለይ በዛው ዓመት መጨረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ገብሬን፤ መንግስቱ ለማና ጸጋዬ ገብረመድህን ጨምሮ ሌሎች በወቅቱ በግጥም ሥራቸው የታወቁ ጥበበኞች በታደሙበት መድረክ ባቀረበው ግጥም በልዩ አጻጻፉና በዜመኛ አነባቡ ያልተደነቀ ታዳሚ እንዳልነበረ በወቅቱ ፕሮግራሙን የቀረጸው ጋዜጠኛ ወርቁ ተገኝ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

የገብረ ክርስቶስ ግጥሞች ከምናውቃቸው ከመደበኛዎቹ የግጥም ቤት አሠላለፍ የተለዩ ናቸው፡፡ በተለይ ግጥም የግድ ቤት መምታት አለበት ወይም የለበትም በሚል በወግ አጥባቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና በተቃራኒው በተሠለፉ እንደ ገብረ ክርስቶስና ሰለሞን ደሬሳ ያሉት የሚነሳው ሙያዊ ክርክር በልዩነት ሲቀጥል በማንኛውም ደረጃ በሚጻፉ ግጥሞች የሚነሱ ጭብጦች፤ የሥንኝ ትስስር እንደዚሁም የመነሻና መድረሻ ስንኞችን የሚደግፉ ሀሳቦች ይዘት መቸም ቢሆን ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡

ገብረ ክርስቶስ በሀሳቡና በስሜቱ ተፈትለው ባጌጡት ስራዎቹ የምንደነቀውን ያህል፤ ከአስተዋይነቱ፣ ከመልካም ሰብእናውና እንደዚሁም ከጠንካራ ሠራተኝነቱ የምንማራቸው ብዙ ቁምነገሮች አሉ፡፡ የተወልን ሥራዎቹ ውርስ ሆነው ለሁልጊዜም አብረውን ይኖራሉ፡፡ ገብረ ክርስቶስን በስዕል ሥራው ዓለም አውቆታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ለስሜቱም ቢሆን፤ በማጣትና በማግኘት፣ በሞት ጭካኔ፣ በብቸኝነት፣ በትካዜና ፍቅር በአጠቃላይ በሠው ልጅ ጠባይ ተለይተው የሚነሱ ማንነቶችን ነቅሶ… በግጥም የተወልን ሥራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ናቸው፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር የገብረክርስቶስ ደስታ አዲስ ናቸው፡፡ በዛ ዘመን ከተነሱ አስደናቂ ብእረኞች ተወዳደሪ ናቸው፡፡ ነገር ግን በቅጡ ለመዘከር የበቁት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይሄ አስደናቂ ሰው ለአገሩ የነበረውን ፍቅር “ኢትዮጵያ እናቴ“ ሲል በሰጣት ቦታ የአገሩን ናፍቆት “አገሬ“ “እንደገና“ በተሰኙ ግጥሞቹ እንደዚሁም የአገር ቁጭቱን “የፆም ቀን“ እና “በባእድ አገር“ በተሰኙት ግጥሞቹ በሚገባ ገልፆታል፡፡ በተለይ አገሬ የተሰኘው ግጥሙ አንጀት ይበላል፡፡ ይህ ታላቅ ሰው በስደት እንደማሰነ የአገሩን አፈር ለመቅመስ አለመታደሉ ያስቆጫል፡፡

‹ሚስጥር›

ሁሉ እንደዘበት

ሁሉም በዘልማድ

ሁሉም እንዲያው እንዲያው

የሚሆን መስሎሃል::

ጉንዳንን ተመልከት

የወፍ ቤትን አጥና

ንቦችን አስተውል

አንድ የውሻ ጩኽት ሙዚቃ እየሆነ…

ዓለምን ያነጋል፡፡